መዋዕለ ህፃናት ተማሪ እያለሁ ሰርካለም ከምትባል ልጅ ፍቅር ያዘኝ። ሰርካለም ጠየም ያለች፣ ክብ ብድንቡሽ ያለ ፊት ያላትና ከሁሉ በላይ ይማርከኝ የነበረው የተዘናፈለ ፀጉሯ ድምቅ አድርጎ በትዝታ ማህደሬ የከተባት እንስት ነች።አሰላ ከተማ በ1980ዎቹ ከዋና መንገድ ውጭ የአፈር መንገዶች ብቻ ነው የነበራት። መዋለ ህፃናት ለመድረስ በፀሀይ አቧራ፣ በዝናብ ደሞ ጭቃ እየታገልን ነበር የምንሄደው። የመማሪያ ክፍላችን የእንጨት ወንበርና ጠረጴዛ የሞላት ነች። በአንዷ አግዳሚ ወንበር ሶስት ሆነን እንቀመጣለን፣ ከፊታችን የእንጨቷ ጠረጴዛ ላይ ደብተራችንን አስቀምጠን እውቀትን እንቀዳለን። የኔ ጠረጴዛ ደብተር ብቻ አልነበረም ምይትይዘው። ከፊት ለፊቴ የምትቀመጠው የሰርካለም ጥቁር፣ ረጅም እና ዞማ ፀጉር ማረፊያም ነበረች። "ሀ...ሁ...ሂ..." እያሉ እኩዮቼ ፊደልን ሲቆጥሩ እኔ ሰርካለምን ከኋላዋ ሆኜ እያየኋት የፍቅርን ሀሁም ጨምሬ እቆጥር ነበር። አንዳንዴ ግን ፍቅሬ ካቅም በላይ ይሆንና ማየቱ ብቻ አልበቃ ይለኛል። እጄን ሰድጄ ፀጉሯን እዳብሳለሁ። ስሟን የማላስታውሳት ፊደል አስቆጣሪያችን ብዙ ግዜ እጅ ከፍንጅ ይዛኝ አቢዎታዊ እርምጃ ወስዳብኛለች። ግዜው ገና ደርግ የወደቀበት ነው። እንደዛሬው ልጅ ማሞላቀቅ አልተጀመረም። በአርጩሜ ቂጤን ተገርፌ እያለቀስኩ ወደ ቦታዬ እመለሳለሁ። ሰርካለምም ቀስ ብላ ትዞርና በአይኖቿ ታባብለኛለች። ለእረፍት ስንወጣ አብራኝ ትጫወታለች። ልጅ እያለሁ በጣም ኩል ነበርኩ። ቢሆንም ግን የሰርካለምን ፍቅር እንዴት እንደምገልፀው ምንም ፍንጭ አልነበረኝም። መጫወቻ ቦታው ላይ አንዴ ከሸርተቴ አንዴ ከዥዋዥዌ እየገፈተርኩ ጥያታለሁ። ስታለቅስ ውስጤ ይንሰፈሰፋል። እሷም ፍቅሬን የምገልፅበት መንገድ መሆኑ የገባት ይመስል ቂም አትይዝብኝም ነበር። Ephrem Zewge ወይም ቤቢ ያጎቴ ልጅ እንዲሁም የትምህርት ቤት ጓደኛዬ እና ወንድሜ ነው። ሰርካለምም ልክ እንደኔው ቤቢ አይነት ጓደኛ ነበረቻት። ስሟ እመቤት ይባላል። ሰርካለምና እመቤት እንደ ትልቅ ሰው ተቀምጠው ማውራት ይወዳሉ። በጣም የተረጋጉ ናቸው። እኔና ቤቢ ደሞ ቀዥቃዣ ሆነን ነው የተፈጠርነው።የትምህርት ቤታችን ሰፊ ግቢ በሳር የተሞላ ነው። ረጃጅሙን ሳር ከቤቢጋ እንደ ፀጉር እየከፈልን አናቱን እንቋጥረዋለን። ቋጥረን...ቋጥረን...ቋጥረን ስናበቃ እየሮጥን እንሄድና ሰርካለምንና እመቤትን "ኑ እንጫወት" ብለን እንጠራቸዋለን። በንፁህ ልብ አምነውን እየሮጡ ይከተሉናል። የተቋጠሩት ሳሮችጋ ስንደርስ ዘለን እናልፋቸዋለን። ሰርካለምና እመቤት ግን ተጠልፈው ይወድቃሉ። ያኔ ከት ብለን እንስቃለን። በውስጤ ግን "ተጎድታ ይሆን፣ ስትወድቅ አሟት ይሆን...ወዘተረፈ" እያልኩ በስስት እጨነቅላት ነበር። የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት በመስከረም ተጀምሮ፣ የበጋውን ፀሀይ አቋርጦ በክረምት ዝናብ ታጅቦ ተጠናቀቀ። አብረውኝ ይማሩ የነበሩ እንዲሁም ታላቅና ታናሽ ወንድሞቼን ጨምሮ የሰፈር ልጆች ሁሉ በሰርካለም ፍቅር መረታቴን አወቁ። በቡድንና በተናጠል "የሰርካለም ባል" እያሉ ይሳለቁብኝ ያዙ። እኔም ላይ ላዩን የተናደድኩ እየመሰልኩ በልቤ ግን እቦርቃለሁ። ክረምቱን በናፍቆት አሳለፍኩ። መስከረም ጠብቶ አንደኛ ክፍል ለመግባት በቀኝ እጃችን ግራ ጆሯችንን መንካት ስንለማመድ የሰርካለም አለንጋ ጣቶች ውል ይሉኛል። ወደ መዋለ ህፃናት እንሄድበት የነበረውን መንገድ ባየሁት ቁጥር "አሁን አሁን" ይለኛል። "የሰርክዬ ባል" ሲሉኝ ደስ ይለኝ የነበረው በሀምሌና ነሀሴ የናፍቆት ረሀብ ወደ ብሶት ይከተኝ ጀመር። ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ መስከረም ጠብቶ አንደኛ ክፍል ገባሁ። ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ አይኖቼ ያለመታከት ሰርካለምን ፍለጋ ተንከራተቱ። ግን አላገኟትም! ሳምንታት አለፉ ወራት ተቆጠሩ ሰርካለም ግን የለችም። ምክንያቱም እኔ "ሀምሌ 19" ት/ቤት እሷ ደሞ "ሚሽን" ነበር አንደኛ ክፍልን የጀመርነው። በትምህርት ቤቶቻችን መሀል 1.5 ኪ/ሜ ያክል ርቀት ነበረ። ሰርካለምን የተራቡ አይኖቼ ዳግም እንዳያዩዋት ርቀት ገደባቸው። ፀጉሯን መዳሰስ የለመዱ ጣቶቼ በናፍቆት ቀጨጩ። ግዜ በመዳፉ እየዳሰሰ እስከሚፈውሰኝ ድረስ ልቤ እንደተሰቀለ ናፍቆት እያራደኝ ከረምኩ። በስተመጨረሻ ግን ለራሴ እንዲህ አልኩ "አንድ ቀን እንገናኛለን።" ከዛ ግዜ በኋላ የስቃይ ዘመኔ አበቃ። ተስፋ ፈውስ ሆነኝ። የሰርካለም ፀጉር በህይወት ዘመኔ ሁሉ ካየኋቸው ፀጉሮች የተለየ እና ውብ እንደሆነ እስካሁን በልቤ አለ። አስካሁንም በፀጉር ውበት ደንግጬ አላውቅም። ከሰርካለም በኋላ ፀጉር🙏🙏🙏