ሰርካለምጋጋ ከአራት አመታት በኋላ ተገናኘን...አዲሱ መሳይ ወይም በሰፈር ስሙ አባቱ የልጅነት ጎረቤቴ፣ ጓደኛዬ እንዲሁም ባላንጣዬ ነው። በሰፈራችን ውስጥ በእድሜ፣ በቁመና፣ በስነ-ልቦና እኔና አባቱ ለረጅም ግዜ ተመጣጣኝ ነበርንና በጨዋታም በፀብም ፍጭታችን ማለቂያ የሌለው ነው። ታላላቆቻችን "ትፈልገዋለህ" "ትችለዋለህ" ምናምን እያሉ ነፃ ትግል ሲያፋልሙን የኔና የአባቱ ድብድብ በገላጋይ ነበረ የሚያበቃው። ታላላቆቻችን "ሁለታችሁ መከባበር አለባችሁ! ይዋጣላቹ!" እያሉ በጣም ብዙ ግዜ አታግለውናል። ነገር ግን "አልፈልገውም፣ አልችለውም..." የሚል ቃል ከሁለታችንም አንደበት ሳይወጣ "ትፈልገዋለህ?" ስንባል "ይምጣ ይምጣ!" እየተባባልን ስንፋለም ኖርን። ባላንጣነታችን በነፃ ትግል ብቻ አልነበረም። አንዳንዴ በጨዋታ መሀል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በንግግር መፍታት ይሳነንና ወደ ሀይል እርምጃ እንገባለን። ተናንቀን ስንደባደብ ዳግም መተያየት የምንችል አይመስልም ግን (እዚጋ "ግና" ልል ነበር ግና ሙድ እንዳይያዝብኝ ብዬ የተለመደውን "ግን" ተጠቅሜያለሁ) ጠዋት ተፋልመን ከሰአት ቆርኪያችንን ከከንችጋ በፌስታል ይዘን ደርኒ ለመጫወት ከቤታችን ብቅ ብቅ እንላለን። በጨዋታው መሀል እንደገና እንጣላለን...እያለ ይቀጥላል። በአጭሩ በስነፅሁፋዊ አጠራር አባቱ የኔ "ኔሜሲስ" ነበር።የአስራ አንድ አመት ልጆች ሳለን (በስዕሉ ላይ በግልፅ እንደሚታየው) በሰፈራችን የምታልፍ አነስተኛ የውሀ ቦይ ከዝናብ ያጠራቀመችውን ውሀ በጭቃ መገደብ ጀመርን። የግድቡ ስራ ሲጀመር ፍቅራችን ደርጅቶ ነበርና አባቱ በአስር ሳንቲም የገዛቸውን ሁለት ድቡልቡል ማስቲካዎች ከኪሱ አወጣ። አንዷ ቢጫ ሌላኛዋ ደሞ አረንጓዴ ነበሩ። አይኑ ስር አስጠግቶ ከተመለከታቸው በኋላ "እንካ" ብሎ ቢጫውን ሰጠኝ። ማስቲካችንን እያመነዠግን በተነቃቃ መንፈስ የግድቡን ግንባታ ማሳለጥ ጀመርን። ግድቡን ከዳርና ዳር ጀምረን ከሁለቱም አቅጣጫ ወደመሀል እየገነባን መሀል ስንደርስ። "መሀሉን ከደፈነው ውሀ እየሞላ አያሰራንም ስለዚህ መሀሉ ክፍት እንደሆነ ይቆይና ሌላው ሲያልቅ እንደፍነዋለን" አልኩት። አባቱ ተበሳጨ! "እንድፈነውና ማስተንፈሻ ከታች እንበሳለታለን" አለ። የቀጠለው የቃላት ምልልሳችን፡እኔ፡ ብንበሳለትም ከታች ጀምሮ ማስተካከል አንችልም ውሀው ያስቸግረናልአባቱ፡ ችግር የለም እኔ እሰራዋለሁ እኔ፡ አብረን ነው ምንሰራው አባቱ፡ አንተ ባልከው ብቻ ነው እንዴ ምንመራው እኔ፡ ግድብ እንደዚ ነዋ የሚሰራው አባቱ፡ እንደውም ካንተጋ አልጫወትም! ለብቻዬ ግድንግድ ግድብ እሰራለሁ ወዲያው (በስዕሉ በጉልህ እንደሚታየው) ከኔ ዝቅ ብሎ እንዳለው "ግድንግድ" ግድብ መገንባት ጀመረ። ግድቡን ከኔ ግድብ ስር ነው የሚሰራው። አላማው ብዙ ውሀ ሞልቶ የኔን ግድብ ማጥለቅለቅ ነው። ስለዚህ እኔ ግድቤን በፍጥነት ጨርሼ ውሀውን ያዝኩበት። ጭቃውን ቆልሎ ከዳር ዳር በደንብ አደራጅቶ የገነባው ግድብ ካለውሀ ባዶውን ቀረ። የኔ ግድብ መሙላት ሲጀምር ከታች በትንሹ ማስተንፈሻ አበጅቼ ውሀ ለቀኩለት። እሱ ግን "ውሀው አይበቃኝም ጨምር" የሚል ጥያቄ አነሳ። እኔም ለታችኛው ተፋሰስ ተጨማሪ ውሀ ለመልቀቅ ካሳ እንደምፈልግ ገለፅኩለት። የተጠየቀው ካሳ ደግሞ ተጨማሪ ባለ አምስት ሳንቲሟ ማስቲካ ነበረች። አባቱ በመደራደሪያ ነጥቡ ክፉኛ ተበሳጨ፣ በገነ! ወዲያው "ማስቲካዬን መልስልኝ!" አለ። "ይሰጥሀል" ብዬ እስከምትጎሳቆል የኘኳትን ማስቲካ ከአፌ አውጥቼ ሰጠሁት። ተቀብሎኝ ጎረሳት። "ጣዕሙን መልስልኝ፣ ይሄ ምንም አይጣፍጥም። የሰጠውህ ከነ ጣፋጩ ነው። ጣእሜን መልስ" አለ። የዚህን ግዜ የታችኛው ተፋሰስ ባለግድብ ጦርነት እንደፈለገ ገባኝ። "ሳይመታኝ ቀድሜ ልምታው" ብዬ በማሰብ የመጀመሪያውን ቡጢ ፊቱ ላይ አሳርፌ ለፀብ ተቀሳሰርኩ። ነገር ግን ጉዳዩ ባላሰብኩት አቅጣጫ አመራ። አባቱ ለቡጢው መልስ ከመስጠት ይልቅ እያለቀሰ ለእናቴ ለመናገር እና ጉዳዩን ቀጠናዊ ለማድረግ ተንቀሳቀሰ። "እሺ በቃ ጣዕሙን እመልስልሀለው፣ ስኳር አመጣልሀለው፣ ሁለቱም ግድብ ያንተ ነው...ወዘተረፈ" እያልኩ ተማፀንኩት። እንዳልሰማ ሆኖ እያለቀሰ አሳጣኝ። በዚህ የዲፕሎማሲ ስራው እኔ ቁጣ እና ማዕቀብ ሲወርድብኝ እሱ የአስር ሳንቲም ሂውማኒተሪያን ድጋፍ ተደረገለት። አባቱ እናቴ የሰጠችውን አስር ሳንቲም ሳይነካት አደረ። በነጋታው የክረምት ማጠናከሪያ ለመማር ቅርባችን ያለው መድሀኒያለም ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ ሳንቲሟን መዥርጦ ሁለት ማስቲካ ገዛ። አንዷን እንደሚሰጠኝ ተስፋ በማድረግ መለሳለስ ብጀምርም ሁለቱንም ማስቲካዎች አይኔ እያየ ጎርሶ በኩራት ማኘክ ጀመረ። ደሜ ፈላ! ለአይኔ አስጠላኝ! "አብረኸኝ እንዳትሄድ" ብዬው እየተንደረደርኩ መድሀኒያለም ቤተክርስቲያን ደረስኩ። የመማሪያ ክፍላችን ውስጥ ገብቼ ኋላ ወንበር ተቀመጥኩ። ግብረገብ ሊያስተምሩን በክፍሉ የተገኙት አለቃ መሰረት (ነብሳቸው በገነት ትረፍ) "ትንሽ ልጅ ነህ ከኋላ ምን ታደርጋለህ? ና እዚህ" ብለው ከፊት አስቀመጡኝ። ከፊት ተቀምጬ የአለቃ መሰረትን ግብረ-ገብ እየተማርኩ በሀሳቤ አባቱ ሁለቱን ማስቲካዎች ጎርሶ እያስካካ ጥርሶቹ እስኪፋጩ ሲያኝካቸው ውል እያለኝ እበሳጫለሁ። ወዲያው ደግሞ የአለቃ መሰረት ቃላት ከሀሳብ አለም ይመልሱኛል። በዚህ ሁሉ መሀል አጠገቤ ሰርካለም ተቀምጣ ልብ ሳልል ብዙ ደቂቃዎች አለፈው ነበር። ክው...ብዬ ቀረሁ! ከአራት አመታት በኋላ ሰርካለም አጠገቤ ተቀምጣ አገኘኋት! ወዲያው አባቱ ከነማስቲካው ከአይምሮዬ ተነነ፣ የአለቃ መሰረት ትምህርትም አልሰማ አለኝ! ቀስ ብዬ ተመለከትኳት። መልኳ ተቀይሯል፣ በጣም አድጋለች። ፊቷ ላይ ጠባሳ አየሁ። "ምን ሆና ይሆን? ወድቃ? ወይ እሳት አቃጥሏት..." እያልኩ ህመሟ እስኪሰማኝ ድረስ አሰብኩ። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። እንደ ህፃንነታችን እየገፈተርኩ መጣል፣ ፀጉሯን መነካካት ወይስ "እንጫወት" ብዬ መጋበዝ? እድሜ ክፉ ጋሬጣ ሆነብን። ወይ እንደልጅ ዘለን መጫወት አልሆነልን ወይ እንደ ወጣቶቹ መጀናጀን አንችል። እየተያየን መተፋፈር፣ አይን መስበር፣ ፊት ማዞር ሆነ። አንዲት ቃል ሳንተነፍስ በአይን አሰባበር እየተናበብን ቀናት ከዛ ሳምንታት አለፉ። የመድሀኒአለም ቤተክርስቲያን የክረምት ትምህርት በሰርካለም ምክንያት ወደድኩት። አንድ ቀን ግን ከትምህርት ቀረች። "ታማ ይሆን? ምን አገኛት?" እያልኩ ሳሰላስል ዋልኩ። ሰርካለምን ለማየት የተሰጠኝ የመጨረሻው እድል ጊዜው ማለቁን አላወኩም ነበር። ከዚያች ቀን በኋላ እስከዛሬ የት ትሁን የት ትኑር አላውቅም! ድንገት መንገድ ላይ ባያት ግን እንደማስታውሳት ቅንጣት አልጠራጠርም🙏🙏🙏