የመቶ ህልፈተ ህይወት የ (ሀጂ) መሀመድ የጥላቻ ምክንያት አንድ
የመቶ እናት ፋጡማ ኡስማን ትባላለች የመቶ እናት ፋጡማ ኡስማን ትባላለች በዛችዉ ሀሉ ወረዳ የሰርዶ ቀበሌ ተወላጅ ስትሆን የወሎ ተፈናቃይ ቤተሰብ ልጅ ነች ። ክብ ፊቷ በጠይም ዉብ ቅብ የተጌጠ ፤ የአይኖቿ ሽፋሽፍቶች በሀያል የዉበት ባላሙያ የተበጁ ፤ ሰልካካ አፍንጫዋ ላይ ተደምሮ የፊቷን ቁንጅን አለማድነቅ ይከብዳል። ከሜትር ከስልሳ አምስት ያልዘለለ ቁመቷ አጋማሽ ላይ ቅርፁን የጠበቀ ዳሌ የአረፈባት ፋጡማ መቶን ወልዳ በአመቱ የሀያ ሰባት አመት ጉብል ነበረች።(ሀጂ) መሀመድ ወደዉ እና ፈቅደዉ በትዳር ለተጣመሯት ሴት ፍፁም ተአማኝ ፤ ያላቸዉን ሁሉ ሳይሰስቱ የሚሰጡ አባወራ ሲሆኑ አላህ ለሰጣቸው ለአብራካቸዉ ክፋይም ጥሩ አባት ናቸዉ። እንድያም ሁኖ ሚስት አይበረክትላቸዉም። ልጅም አይሰምርላቸዉም። እጣ ፋንታ ይሉት አይደል?(ሀጂ) መሀመድ ከፋጡማ ኡስማን ጋር መቶ ከመወለዱ በፊት ለአንድ አመት በጣፋጭ ፍቅር ''አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ'' እየተባባሉ ኑረዋል። ከመቶ መወለድ በኋላም የከፋ ግጭት ባይኖራቸውም ጥቂት ጥርጣሬ የሚጭሩ የዉስልትና ባህሪዎችን ፋጡማ ማሳየት መጀመሯ (ሀጂ) መሀመድን ቅር እያሰኘ መጥቷል ። ከዕለታት በአንዱ ቀን (ሀጂ) መሀመድ ብልታቸዉ ላይ ያለተለመደ ህመም ይሰማቸዉ ጀመር። ህመሙ ይሽር ይሆን ሲሉ ቀናትን በትዕግሥት ቢያሳልፍም በሽታዉ እየበረታ ጠረን ያለዉ ፈሳሽ ማስከተል ጀመረ። እናም ችግሩ ፀንቶ ቢችሉ የታገሱትን ፤ ሲብስ ሊታከሙት ከሀኪም ደጅ ፀኑ። እንደ ህመምተኛ ተራቸዉን ጠብቀው የበሽታቸዉን ምንነት ተረዱ። መርዶዉን ላለማመን ሀኪም ቤት ቀየሩ። ቤቱን ብቻ ሳይሆን ሀኪም እየቀያየሩ የዉጤቱን መለወጥ አብዝተዉ ተመኙ። ሊሆን ግን አልቻለም። ''ጨብጥ ጨብጦ አባላዘር አመንዝር ሽርሙጥና ክህደት እኮ ጨበጥ ጨብጦ ፋጡማ ጨብጦ ፋጡማ አመነዘረች ያንን ቂጧን ወንድ ስር .......... የሆነ ወንድ ናቀኝ ፋጡማ ከሀዲ''..። የ (ሀጂ) መሀመድ አዕምሮ ዉስጥ በፍጥነት ፤ በአንደበታቸው ደግሞ በለሆሳስ የሚመላለሱት እነዚህ ቃላት ከህክምና ጣብያዉ እስከ ቤታቸው ባለዉ የ800 ሜትር ርቀት ዉስጥ ከ200 ሜትር በላይ በዝግመት እና በለሆሳስ መቀጠል አልቻለም ። ''ጨብጥ ጨብጦ አባላዘር አመንዝራ ሽርሙጥና ክህደት እኮ ጨበጥ ጨብጦ ፋጡማ ጨብጦ ፋጡማ አመነዘረች ያንን ቂጧን ወንድ ስር .......'' ሰዉ ሀሉ ከየቤቱ እየወጣ '' እሄ ሰዉየ ለየለት'' እያለ እስኪመለከታቸዉ ድረስ ቃላቶቹን ከፍ አድርገው እየደጋገሙ ወደ ቤታቸው ሮጡ። በአስፓልቱ እና በሱቃቸዉ መሀል የተዘረጋዉን የእንጨት ድልድይ ለግዜው መጠቀም አላስፈለጋቸውም ። አንዳች መግነጢሳዊ ሀይል ወርዉሮ ከሱቃቸዉ መስኮት አላተማቸዉ። ከመቅስፈት በግጭት ተነድሎ ደም የሚተፋ የግንባራቸዉ የግራ ክፍል የትኩረት አቅጣቸዉን ማስቀየር ቢችል መልካም ነበር። ነገር ግን በፍጹም ሊሆን አልቻለም። ፋጡማ እና ጨብጦ ፤ ሽርሙጥና እና ክብረቢስነት። የአዕምሮዋቸዉ ሀሳብ አሳላጭ ክፍል ከነዚህ ቃላት በቀር ስንቁን ተነጥቋል ። በስስ ዲርያ የተሸፈነችዉ ፋጡማ ጉዷን ተረድታዉ ቢሆን ከሰዓታት በፊት ሰላም የነበረ የሚመስለዉን ግና ሰይጥኖ ሊበላት የመጣ አባወራዋን ቁማ ባልጠበቀችዉ ነበር። (ሀጂ) መሀመድ እቤታቸው ገብተዉ ፋጡማን በሰፊዉ መዳፋቸው በጥፊ አላግተዉ ከምንጣፍ አልባዉ ወለል አገናኟት። ከስር ኮረኮንቻማዉ ምድር እና ከላይ የቀወሱት (ሀጂ) መሀመድ ተጋግዘዉ የፋጡማን ስስ ቆዳ እንደ ሽንኩርት ይልጡት ጀመር። እቤት የጀመረዉ ዱላ ደጅ ድረስ አርቆ የፋጡማን ስጋ አንገላታዉ። (ሀጂ) መሀመድ ፋጡማ ላይ ጨክነዉ መሬት ላይ እየጎተቱ በመሀል ከተማዋ ወደ ተንጣለለችዉ ትንሽዬ አደባባይ ላይ ወርዉረዋት ከላይ የለበሱትን ሸሚዝ እና ከስር ያገለደሙትን ሽርጥ በእብደት አዉልቀዉ እርቃናቸውን መለመሎዋቸዉን እየወዘወዙ '' አንቺ ሸርሙጣ እሄ አንሶብሽ ? እሄ ለኡካ ህዝብ የሚበቃ..... ትዳሬን ብዪ በኖርኩ ?'' እያሉ የፋጡማን ልብስ ከላይዋ ቀዳደዉ እርቃኗን አስቀሯት። (ሀጂ) መሀመድ በአደባባይ የወሲብ አቅማቸውን ለጠላቶቻቸው ለማሳየት የሚወዷትን ፋጡማ ትግል ገጠሙ። ግና እንደፊልም ሲመለከቱዋቸዉ የነበሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ሁለት የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶችን ተከትለው (ሀጂ) መሀመድን የመገላገያ ድፍረት በማግኘት ቀጣይ እርምጃቸውን መግታት ቻሉ። በዚህ ግርግር ብጫቂ ጨርቅ ሀፍረቷ ላይ ጣል አድርጋ ፋጡማ አመለጠች። ከዝያ ቀን በኋላ ፋጡማን ሰማይ ይዋጣት ምድር የሚታወቅ ነገር የለም። (ሀጂ) መሀመድም አላፋለጓትም። እኔነኝ ባይ ፋጡማን (የመቶን እናት) የበላ ጅብም አልተገኘም። በዚህምክንያት ይመስለኛል (ሀጂ) መሀመድ መቶ እና ፋጡማ ይመሳሰሉባቸዋል። ፋጡማ ኡስማን እና መቶ ኪሎ ወርቅ።አሀሀሀ ፋጡማ ሸርሙጣዋ እና መቶ ኪሎ ሰገራ። እያደር መቶ በጉስቁልና የህፃን መልኩ እየረገፈ ፣ እድገቱ ቁልቁል ሁኖ መከራ በረከቱ እንደሆነ ቀረ። ሁለት አመታትን በቸነፈር እና በጉስቁልና ያሳለፈው መቶ በድሎት የጀመረዉን አለም በሰቆቃ ሊሰናበተዉ አይቀሬው ቀን ደርሶ ላይመለስ ሄደ። ያን ዕለት መቶ ህይወቱ የአለፈዉ በግምት 12 ስዓት አከባቢ ነበር። በከተማዋ መብራት የለም። ከተማዉ ጭር ብሏለል። የመቶን ህልፈት ሰምተን ወደ (ሀጂ) መሀመድ ቤት ያቀናነዉ እኔ አና ሞልጌ (ሙሉጌታ) ነበርን። (ሀጂ) መሀመድ ከሱቃቸዉ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብለዉ እንደወትሮው ይቆዝማሉ። አስክሬኑ ደግሞ እቤት ዉስጥ አርፏል ። ጠጋ ብለን አስክሬኑ መገነዙን ጠየቅናቸው ። ''መብራት እንደሌለ እያያችሁ በምን እንድገንዘዉ ፈልጋችሁ ነዉ የምትጠይቁኝ? ደንቆሮ ናችሁ ልበል?'' ባትሪስ የለም? የሚሸጥ ብቻ ነዉ ያለዉ። እሺ ዋጋዉ ስንት ነዉ? ''ከነ ድንጋዩ 12 ብር ። እዚሁ ተጠቅማችሁ የምትመልሱት ከሆነ በግማሽ እሰጣችኋለሁ ። በ6 ብር ዉሰዱት።'' (ሀጂ) መሀመድ መክፋት ከፈለጉ እንዲህ ናቸዉ። በ6 ብር ባትሪዉን ገዝተን አስክሬኑን ገንዘን ባትሪዉን ከመለስንላቸዉ በኋላ አስክሬኑ ጎን ቁጭ ብለን እንደወትሮው ጄን እና ኡዞዋችንን እየጠጣን ስንጫወት አምሽተን ወደየቤታችን አመራን። በንጋታው በእስልምና ስርዐተ ቀብር መሰረት መቶን አፈር ለማቅመስ በስፍራዉ የተገኘነዉ ከሰላሳ ሰዎች አንበልጥም። (ሀጂ) መሀመድ የአንደመቱን ህፃን አንበላቸዉን እሽኮኮ ተሸክመው የወንድሙን የመቀበርያ ጉድጓድ ቁልቁል እያሳዩት ''አምበላቸዉ! አየኸው ? መቶ ሙቷል። ጉርጓድ ገብቷል ። ዳግመኛ እንዳትጠይቀኝ'' እያሉ ደጋግመው ይነግሩታል። በወግ አግብተው ከወለዷቸው ልጆቻቸው ሁሉ ገዝፎ በዉል ስሟን እንኳን ከማያስታዉሷት ባይተዋር ሴት የወለዱትን ልጅ የልጆቻቸው ሁሉ አምበል ያደረጉትን አምበላቸዉን ከሚገባው በላይ ይወዱታል።................(ሀጂ)መሀመድ። ተአምረኛው ሰዉ። ከቀብር መልስ ከሦስት የማይበልጡ የጎረቤት ሴቶች የወጉን ቡና አፍልተዉ ጠብቀዉን ነበር። (ሀጂ) መሀመድ ግን በሁነቱ የተደሰቱ አይመስሉም። ከደጃቸዉ ጥቂት እንደተቀመጥን በከተማዋ የከበሩ አንድ ትልቅ እናት ነጠላቸውን ዘቅዝቀው ገና ከርቀት ዋይታቸዉን እያሰሙ ተቃረቡን። ከለቀስተኞቹ መሀል የተሰማዉ የዉግዘት ናዳ ግን ሀዘንተኛዉን አንገት ያስደፋ ፤ ክብርት አልቃሽ ወይዘሮዋን ደግሞ አዋርዶ ያባረረ ተግሳፅ ሁኖ ከፍ ሲል ተደመጠ። (ሀጂ) መሀመድ ነበሩ። አወዛጋቢው ሰዉ። ''ዝም በይ አንቺ ቅሌታም። ዛሬ መቶ ሲሞት መጣሽ? አንድ ሲኒ ወተት ጠፍቶ አንጀቱ ተአጥቦ እንደተጨመቀ ፎጣ ሲጠቀለል የት ነበርሽ? የአዋቂ ምግብ ከብዶት ሬንጅ ሲያስቀምጠዉ በዱንያ የተሞላው እቤትሽ ርጋፊ የአጥሚት ዱቄት መሰንዘር የተሳነዉ ቤት ባለፀጋ ሴት ምን እግር፧ ጣለሽ እቴ? እንደዉ ዛሬ አዛኝ ቅቤ አንጎች ፤ የዝሆን እንባ ታነቢ እምፈቅድ የመስልሻል? '' ሰዉነታቸዉ ሁሉ ይወረገረጋል። ከንፈራቸዉ ይንቀጠቀጣል። ''ሁላችሁም አንድ ናችሁ።'' እቺን ቃል እንደተናገሩ አንገቴን እግሮቼ መሀል ቀብሬ አዳምጣቸዉ ገባሁ። ''የሰዉ ትዳር የምታፈርሱ ሴሰኞች። በሰዉ ማግኘት አይናችሁ ደም የሚለብስ ምቀኞች። የተቸገረን ችጋራም አድርጋችሁ የምትመፃደቁ ከንቱዎች ። ለገዛ ዘመዳችሁ የማትሳሱ ሟርተኞች። ስልጣንን ለመጨቆኛ እና ለዘረፋ ፤ ሀይማኖትን ለሴራችሁ መሸሸጊያ የምትጠቀሙ ስብዕና የተባለ ነገር ያልተፈጠረባችሁ በድኖች ናችሁ'' ''እድፋችሁን በጨርቅ ሸፍናችሁ የመሀመድን ጭቃኔ በመቶ ሞት እያዋዛችሁ ልታወሩ ተቻኩላችኋል አይደል? ግቡ እና በየስልቻችሁ ስር አሸኩሽኩ። ትዳሬን በተደጋጋሚ ቀምታችሁኛል። ሰርቼ እንዳልለወጥ ዘርፋችሁኛል። ከለጆቼ ነጥላችሁኝ ስታበቁ በርህራሄ ልታነቡ?........ ወላሂ ብላሂ ቀለደኞች ናችሁ። መቶን በክፋታችሁ ገመድ አንቃችሁ ገድላችሁት አልቅሳችሁ ልትቀብሩት አላህ ፊት በድፍረት የቆማችሁ አይን አዉጣዎች። ወለሂ አላህ ይህንን በደል የማይመለከት አይነ ስዉር አይምሰላችሁ ። ቀን ጠብቆ በየመስፈርያችሁ የየድርሻችሁን ያቀብላችኋል ። ክፉዎች፣ክፉዎች ናችሁ...'' (ሀጂ) መሀመድ ድምፃቸዉ እየረገበ መጣ። ከአቀረቀርኩበት ቀና ብዬ አከባብዬን ስመለከት አንድም ሰዉ አጠገቤ አልነበረም ። ሁሉም ነጉደዋል ። (ሀጂ) መሀመድ በግራ እጃቸዉ ላይተር ይዘዉ ፣ በቀኝ እጃቸዉ ከግራ የሸሚዝ ኪሳቸው ሲጋራ ለማዉጣት ይታገላሉ ። ከስር ከዕግርጌያቸዉ የህፃን ፊቱን አኮሳትሮ አባቱን በጥሞና የሚከታተለዉ አምበላቸዉ እይታዉ ፍፁም ቅኔ ነበር። ሰሙ ያልገባኝ ፣ ወርቁ የተሰወረኝ ቅኔ። የወለዬዉ የ(ሀጂ) መሀመድ ህፃን የአምበላቸዉ ቅኔ እዲህ የሚል ይሆን? 'ነጭናጫዉ አባቴ ላይደግም የሚገድል ለመግደል ይደማል ፤ ቢገድሉት ይሞታል ይህን ሆደ ባሻ እሄንን ርህሩ ሰዉ በምን አባብተዉት በምን ይገድሉታል?'' ///////////////////////////