መቶ እና አምበላቸው የ(ሀጂ) መሀመድ ልጆች።
ሀገረ ወሎን ከምንም በላይ ይወዷታል። የወሎው ድርቅ ፍጥረት ከፈጣሪው የተጣላበት ፤ ፈጣሪም በፍጥረቱ የጨከነበት ክስተት እንደነበር በክፉ ትዝታ የሚያስታውሱት (ሀጂ) መሀመድ የእርሻ ሰንጋቸዉ የሚግጠዉ አጥቶ ቀይ አፈር ሲልስ በአይናቸው በማየታቸዉ የመንግስትን የሰፈራ ዕቅድ ለመቀበል የተገደዱ ቢሆንም የሰፈራዉ ቦታ ኢሉአባቦር መሆኑን ቢያቁ እግራቸውን እንደማያነሱ ይናገራሉ። ''ምነዉ ? ለምን'' ለሚላቸው ደግሞ ''በለምለሟ ኢሉባቦር በክፋት የተሞሉ ሰዎች እንደሚኖሩባት ጥናት ነበረኝ'' ሲሉ አጭር መልስ ይሰጣሉ ። በዚህች በሜማረሩባት ሀገር ብዙ ሰርተዉ ብዙ አግኝተዋል ፤ ብዙ አግብተዉ ብዙ ፈተዋል ፤ ብዙ ወልደዉ መቶ እና አምበላቸው በሚባሉ የአራት እና የአንድ አመት ልጆቻቸዉን ያለ እናት እያሳደጉባት ይገኛሉ። በዛ ጠራራ ፀሀይ ከሱቋ በረንዳ ላይ እንደ ሬንጅ እየቀለጠ እሪታዉን የሚያቀልጠዉን የአራት አመት ህፃን(መቶን) በመብረቃዊ ቁጣና እናት ተኮር አፀያፊ ስድቦችን አዉርደዉበት አፉን ካስያዙት በኋላ ህፃኑን አምበላቸዉ በፍጹም አባታዊ ርህራሄ አባብለዉ ዝም አሰኙት። .......ሁለት ጥግ በረገጡ ማንነታቸው ግራ ተጋባሁ ። አንደኛዉ ልጃቸው ላይ ሰይጥነዉ ሲያበቁ ለሌላኛው መላዕክ ሁነዉ አገኘኋቸው ። ግን ለምን ? ከጥቂት ዝምታ በኋላ መወዛገቤን በጥያቄ ማጀብ ጀመርኩ ሁለቱም ልጆቿ ናቸዉ? አዎ የትልቁ ስሙ ማነዉ? መቶ ትንሹስ? አምበላቸው መቶ ማለት ምን ማለት ነዉ? ሲወለድ መቶ ኪሎ ወርቅ ብየዉ ነበር። ጥቂት ተክዘው ሲያበቁ ''ምን ያደርጋል እንደምታየዉ መቶ ኪሎ ሰገራ ሁኖ ቀረ። በሱማ ተስፋ ቆርጭያለሁ። በስሱ ፈገግታ አሳይተዉኝ ''አንዱ ጓደኛዬ ምን አለኝ መሰለህ ?'' ''በመቶ ተስፋ መቁረጥ የለብህም። ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ ነዉ የሚታየኝ ።'' ሲለኝ ''አይ አተክልት ወላሂ ላንተ እኮ ይታይሃል በአላህ ንገረኝ እስኪ ምን እንደሚሆን ? ዶክተር ብርሀኑ ነጋን የሚተካ የሀገር መሪ ይሆናል ብለህ እስኪ አንጀቴን ቅቤ አጠጣዉ'' አልኩት። ''አተክልት? ተወዉ እሱ ቀልደኛነዉ ወዳጄ።'' በግራ እጃቸው የሌለ ፂማቸዉን እየነጩ '' አየኸው? አየኸው? መቶ አፉን ከፍቶ እንዴት ላጩን እንደሚለቀዉ'' ፀሀይ በርትቶበት በከፊል እንቅልፍ እና በከፋ ድካም ወደ ሚሰቃየው ልጃዉ እየጠቆሙ ይነገሩኛል። ''እንዲህ ሲሆን አይቶት እኮ ነዉ። እንዲህ አፉን ከፍቶ ስለሚቀመጥ የባንክ ቤት ብር ቆጣሪዎች ምላሱን ለጣታቸዉ ማርጠብያ ይጠቀሙታል'' ''ብሎ የቀለደበኝ'' ብለዉ ፂማቸዉን እየነቀሉ ከቅፅበታዊ የፈገግ ፊታቸዉ ወደ መደበኛው ኮስታራ ፊት የተመለሱት። ///////// በዚህ መልኩ የጀመረው የኔና የ(ሀጂ) መሀመድ ግንኙነት ከትዉዉቅ አልፎ ከጓደኝነት ገዝፎ ከዝምድና በላይ ተጋምደን አምስት አመታትን አሳለፍን። የ (ሀጂ) መሀመድ ሱቅ ቀን ሸቀጥ የሚሸጥበት ማታ ላይ ደግሞ መጠጥ በችርቻሮ የሚገኝበት ታጣፊ ግሮሰሪ በመሆን ታገልግላለች ። ቀን እሳቸው የሱቅ ስራቸዉን ፤ እኔም ፔሮል የምፈርምባትን ስራ ስንሰራ እንዉል እና ማታ ላይ የሸቀጥ ሱቃቸዉ ዉስጥ እሳቸው ኡዞ እኔ ደግሞ ጂን እንይዝና ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርክታቸዉን ያለመሰልቸት አዳምጣለሁ ። በከተማዋ ከእኔ ዉጪ ጓደኛም ይሁን ዘመድ ብለዉ የሚቀርቡት አንድም ሰዉ የለም። የከተማዋ ሰዎች እንደክፉ አዉሬ ይፈሯቸዋል። እሳቸዉም የከተማዋን ሰዎች እንደ ሀጥያት ይፀየፏቸዋል። ለጥላቻቸዉ ምክንያት የሚሉትን ታሪክ ለአምስት አመታት አስደምጠዉኛል።
ይቀጥላል .....