(ሀጂ) መሀመድ የሱፍ ተአምረኛዉ እና አወዛጋቢው ሰዉ
ክፍል አንድ
መረር ያለና መጥፎ ሊባል የሚችል አይነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ነገሮችን በቀላሉ ማከናወን የሚችሉና ደፋሮች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎችን የመምራትና የፈጠራ አቅማቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ ።ለሰዎች ደግነትንና ጥሩነትን የሚያሳዩ ሰዎች በህይወታቸው ደስታና የእርካታ ስሜትን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ከዚህም ባለፈ ከፍ ያለ የራስ መተማመንና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ይስተዋልባቸዋል።ነገር ግን የጥሩ ሰዎች መገለጫዎች ምንድናቸው? ፍቅር፣ ደግነት፣ የቡድን ሥራ፣ ይቅር ባይነት፣ አመስጋኝነት፣ በሰዎች ስኬት አለመቅናት፣ አሳቢነት ወይስ ለብዙዎች ጥቅም መቆም?(ሀጂ) መሀመድ የሱፍ በበከል ፣ በግመል ስጋ እና በወተት ቅብጥ ብለዉ እንዳደጉ ከዘዉትር ምሬት አዘል ትርክታቸዉ መረዳት ቢችልም በ1977ቱ የድርቅ ችግር ከሀገረ ወሎ ወደ ኢሉአባቦራ ዞን ሀሉ ወረዳ ተፈናቅለዉ የመጡ ተፈናቃይ መሆናቸዉን የግል መሀደራቸዉ ይጠቁማል። ከ(ሀጂ) መሀመድ የሱፍ ጋር የተዋወቅነው በ2002 ዓ.ም በመንግሥት ስራ ኢሉአባቦራ ዞን ሀሉ ወረዳ በተመደብኩባት ኡካ ከተማ ነበር። ኡካ ከተማ ከመቱ ወደ ጋምቤላ በሚወስደው አዉራ መንግድ ላይ ለሁለቱ ከተሞች አማካይ የሆነች ፤ በአሮጌ ቆርቆሮ የተሞሉ ቤቶች እና በነፈሰ ቁጥር በአቧራ የምትሸፈን ትንሽ ከተማ ነበረች። በመሀል ከተማዋ በስተቀኝ በአብዛኛው ፌስታል ፣ አሮጌ ባትሪዎች እና የኮንደም ማስታወቂያ ፊት ለፊት በሚታይባት ትንሽዬ ሱቅ ዉስጥ ጠይም ፣ ቁመተ መለሎ እና ጣቅያ ያጠለቁ በሀምሳዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙ ጎልማሳ ሰዉ ከሱቋ ጎልተዉ ይታያሉ ።ገና ከመኪና ከመዉረዴ የመጀመሪያ እይታዬ መዝገብ ላይ የሰፈሩት እኚህ ሰዉ ነበሩ ። (ሀጂ) መሀመድ። ፊታቸው ላይ በብዛት የሚታየው ነጠብጣባማ ቡጫቂ ኮስታራነታቸዉ ላይ ተጨምሮ ጉስቁልናቸዉን በይፋ ይናገራል። ከሱቃቸዉ መስኮት እንደደረስኩ ''እንግዳ ነህ?'' በማለት ነበር ሰላምታ ለመጠየቅ እንኳን እድል የነፈጉኝ። አወንታዊ ምላሼን ከአፌ ሳልጨርስ የከተማዋን ሰዎች ክፋት ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፣ ዘመድ አልባ ባይተዋር መሆናቸውን ..... ብቻ.... ዉስጣቸዉ ያለዉን ብሶት እና ምሬት ወደ ሱቃቸዉ ጎራ ያልኩበትን ምክንያት እንኳን ሳይጠይቁኝ ካወጉኝ በኋላ እኔም ወደዚህ ሀገር የተላኩት የሆነ ከፍተኛ ጥፋት ባጠፋ እንጂ በሰላም እንዳልሆነ ነግረዉኝ ሲጋራ ለመሎከስ ወሬያቸውን አቋረጡ።የለኮሱትን ሲጋራ በረዥሙ ወደ ዉስጥ ከሳቡ በኋላ በሱቋ ባንኮኒ ትይዩ በምትገኘው መቀመጫ ተደላድለው በመቀመጥ አረፍ የምልበት ሰባራ ጠረጴዛ አቀብለዉኝ ሲያበቁ ወጋቸውን ግን ከሁለት ደቂቃ በላይ ማቋረጥ አልቻሉም ። ይልቅ ከነዚህ መሰሪ የማህበረሰብ አካላት እንዴት መጠንቀቅ እንዳለብኝ ፣ በከተማዋ ተከብሬ ለመኖር መስፈርት ናቸዉ ያሏቸውን ተግባሮች በመደርደር እና ባይተዋርነታቸዉን የተረዳላቸዉ አላህ እኔን እንደላከላቸው በሚያፅናና ቅላፄ እያወሩኝ ሳለ በተመሳሳይ ሰዓት ዉስጥ ከሱቋ ዉስጥ እና ከሱቋ በረንዳለ ላይ የተሰማዉ የህፃናት ለቅሶ ወጋቸዉን አቋረጠዉ።
ይቀጥላል ......