የቀዝቃዛዉ ማስታወሻ ቅፅ 1የምድር ጨው ናችሁ! (ሙሉውን ካላነበባችሁት እቀየማችኋለሁ)
Akaakayyuu Tolasaa ወይም እኛ እንደምንጠራው ሶል ዩኒቨርሲቲ ሳለው ጓደኛዬ ነበር። የካምፓስ ህይወት ደስ የሚለውን ያህል አሰልቺ ገፅም እንዳለው መቼም ያለፈበት ሰው ሳይረዳው አይቀርም። በተለይ እንደሶል አይነት ጓደኛ ከሌለህ የካምፓስ ህይወትህ ዞረህ ማየት የማትፈልገው አስከፊው የህይወትህ ምእራፍ ሆኖ ሊያልፍ ይችላል። እኔና ሶል የካምፓስ ህይወት ድግግሞሽ ጥሰን ለመውጣት ሁልግዜ መንገድ ነበረን። ለምሳሌ አንድ ቀን ከመሬት ተነስተን ስንዘፍን ልናመሽ እንችላለን። በማግስቱ ግን አንደግመውም ወደ መዝሙር እንከረበታለን። አንድ ቀን ገፀ በሀሪያት ፈጥረን እንላበሳቸዋለን። ካራክተር ሳንሰብር ቀኑን እናጋምሰዋለን።አንዴ እንዲህ ሆነ የካፌ ሰልፍ ረዝሞ ጥበቃው አሰለቸን። ስለዚህ ግዜውን ለመግፋት ሁለት የልጥጥ ቤተሰብ ልጆች ገፀ ባህርያትን ፈጠርን። እና የካፌው ሰልፍ ላይ ድራማውን ጀመርን።እኔ፡ ዶላሩን ዘረዘርከው?ሶል፡ ቺኳ ብር ያስፈልገኛል ብላ ዘርዝሬ ሰጠኋት ከዛ አይበቃኝም ጨምር አላለችምእኔ፡ ምን አይነት አይናውጣ ነች! 1000 ብር አንሷት ነው? ሶል፡ በጥፊ ብዬ አጠገቤ እንዳትደርሺ አልኳት በመሀል ከተሰላፊዎች መሀል አንዱ፡ "ሴትን ልጅ በብልሀት ነው መያዝ። መማታት ጥሩ አይደለም" ብሎ ፊቸሪንግ ገባ። በጉዳዩ ላይ እየተወያየን እየተከራከርን ከመቅስፈት ሰልፋች ደረሰ። ሽሯችንን አፍሰን ወጣን! በሌላ ግዜ ደግሞ ወደከተማ ወጥተን ስንዝናና አመሸን። ወደ ግቢ ስንመለስ "ለምን ፀብ አንፈጥርም" ብለን ተማከርን። ታክሲ ውስጥ ሆነን ሶል የፀቡን አጀንዳ ከፈተ። ሶል፡ አምኜህ እንዲ ታረገኝ! ያውም ታናሽ እህቴ ቡቱን! እኔ፡ ሶል እንደምታስበው አይደለም! ምንም የተፈጠረ ነገር የለም! ሶል፡ ዝም በል!!! ደርሼ በአይኔ ያየሁትን ልትክደኝ ነው! ወይኔ ሰሎሞን። ገድዬህ እስር ቤት እማቅቃታለሁ! ድራማው ቀጠለ። ታክሲ ውስጥ የነበረው ሰው ሁሉ ተደናግጦ ቦታ አቀያየሩን። እኔን ከኋላ አስቀመጡኝ። ለሶል ተመቸው። ጮክ ብሎ "በቡቱ ቀልድ የለም! አንላቀቅም! እቃ ገዝቼ እስክመለስ እኮ ነው..." እያለ ዛቻውን ያዘንበዋል። እኔም አጠገቤ ያለውን ሰው "ምንም አላደረኩም! ሲገባ እየተሳሳምን ነበር..." እያልኩ አስረዳለሁ። በዚህ የሀሰት ፀብ የዩኒቨርስቲው 1/4ኛ በለሊት ታመሰ። የዲፓርትመንታችን ልጆች "በለሊት ዶርም መቶ አንድ ነገር እንዳያደርግህ" ብለው ሌላ ዶርም አሳደሩኝ። ሶልም ድንጋይ ይዞ እየዞረ ጉዳዩን ሲያጋግል አመሸ። በማግስቱ ጠዋት ለቁርስ ከሶል ጋር ወደካፌ ስንሄድ ያዩን ሁሉ አብዝተው ተጠየፉን። ምንም ማድረግ አይቻልም። ሙዳችን ነው! አሁን ዋናው ጥያቄ "ሶልን ለምን በጨው ሳልኩት?" የሚለው ነው። በ2000ዓ.ም ሁለተኛ አመት ተማሪዎች ሳለን ብሬክ ደረሰና ወደቤት ለመሄድ ተሰናዳን። ነገር ግን እኔና ሶል ለትራንስፓርት የተላከልንን ገንዘብ አጉድለን ነበርና ቅናሽ የትራንስፖርት አማራጭ መፈለግ ጀመርን። በመጨረሻም ሙዝ ጭኖ ከአርባምንጭ አዲሳባ በሚጓዝ አይሱዙ ቃጥራ (በለሊት) ለመሄድ ወስነን ጉዞ ተጀመረ። ሹፌርና ረዳት ጫት እያመሷኩ በኮካ ያወራርዳሉ። በየደረስንበት ከተማ ሺሻ ያፈነዳሉ። ጉዞው በሳቅና ጨዋታ የፈካ ነበር። አላባ የምትባል ከተማ ለመድረስ አስር ያህል ኪ/ሜ ሲቀረን ግን አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ። ሽፍቶች መንገዱ መሀል ገቡ። ሹፌርና ረዳት በድንጋጤ ተክዚናቸውን ዋጡት! የነሱን ድንጋጤ ሳይ ሰማይ የተፋብኝ መሰለኝ። ሹፌሩ መኪናውን ከመንገድ አውጥቶ መብራትና ሞተር አጠፋፋ። በድቅድቁ ጨለማ ከቁጥቋጦ በቀር ምንም በሌለበት ምድረበዳ ከነብሰ በላዎች ጋር ተፋጠን እራሳችንን አገኘነው። በልቤ "አምላክ ሆይ ነብሴን ተቀበላት" አልኩ። ደመ ነፍስ 'እራስህን አድን' ትልሀለች። ራስህን ማዳን በማትችልበት ሁኔታ ብትሞት እንኳን ከሞት ባሻገር ያለችውን ገነት ለመውረስ ትፍጨረጨራለህ። እኔም ምስኪን ሆኜ "ከሞትኩ ጀነቷን አደራ" ብዬ መማፀን ጀመርኩ። ሶል እንዲህ አለኝ "ልክ ሲመጡ ጠመንጃውን ደግነው ስለሚያሶርዱን ዘልዬ ያንዱን ክላሽ እይዝበታለሁ። ተከትሎት የሚመጣውን በአርማጊ ወይ በቺፍሪጊ መንጋጭላውን እለዋለሁ ሶስተኛ ከመጣ በቹምቹምቻጊ ቹምቢ ልቡን አፈርሰዋለሁ። መሳሪያውን ከቀማሁ በኋላ እራሳቸውን እንቀጠቅጣቸዋለን" አለኝ። ግራ ገብቶኝ እያየሁት ቀጠለ "አንተ የባረቀ ጥይት እንዳያገኝህ እዚህ ስር ተደበቅ" አለኝ። እኔ ገና ሞቼ ገነት ስለመግባት አስባለሁ ሶል በቁሙ ገነት ውስጥ ነበር። በዚያች የጭንቅ ሰአት ሶል እራሱን ከማዳን ይልቅ እኔን ማዳን መረጠ። በእውነቱ ነብሱን ስለወዳጁ አሳልፎ ከሚሰጥ በላይ ፃድቅ አለ? ፈጣሪ ግን ይህ እንዲሆን አልወደደምና በሽፍቶቹ ልብ ፍርሀትን አነገሰ። በቆምንበት ቦታ እንዳለን 20 ደቂቃ ጠበቅን። በስተመጨረሻ የአላባ ፖሊሶች ደረሱልን። አንቦ ያበቀለችው ሶል የአርባምንጭ የሶስት አመት ቆይታዬን እንደ ሶስት ሳምት እንዲያጥርብኝ ካደረጉ ቀና፣ ልበ መልካምና ፃድቅ ሰዎች መሀል አንዱ ነው! ይህን ታሪክ ሳልናገር ባልፍ ፈጣሪም ይቀየመኛል። እንደሶል አይነት ልቦች የምድር ላይ ህይወት ማጣፈጫ ጨዎች ናቸው። ለዚህም ነው ሶልን በጨው የሳልኩት🙏🙏🙏 ኦርጅናሉ ፎቶ እንደሁልጊዜው በግራ የኔና የሶል አንፍር ገድሎች በክፍል ሁለት ይቀጥል ካላችሁ እና የማንበብ ተነሳሽነት ካላችሁ አሳውቁኝ! "ትል አካሄድ"ን እነግራችኋለሁ።