ትል አካሄድ
መጀመሪያ አርባምንጭ ስደርስ አየሩ በጣም ይሞቅ ነበር። ከመኪና ስወርድ እሚገርም ሙቀት! "አማኑኤል ተበላህ" ነበር ያልኩት ለራሴ። (በስዕሉ ያስቀመጥኩት ሲነሪ ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ፊት ለፊት የሚያልፍ መንገድ ነው።) አርባምንጭን ለመጀመሪያ ግዜ የረገጥኩት እዚህች ቦታ ላይ ነው። ከዛ ሶስት አመት ሙሉ ባናና ትሪፕ እያልን የመንገዷን ግራና ቀኝ ይዘን እለት በእለት ተመላልሼባታለሁ። (በስዕሉ በግራ በኩል አንድ ጉብልና አንዲት ኮረዳ ሙዝ ይዘው ይታያል) ይህች መንገድ ስንት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በአይን ፍቅር የተለከፉባት፣ ስንቶች የተጀናጀኑባት፣ የብር አስር ሙዝ ገዝተን አንድ ያስመረቅንባት፣ የጋሞ ጎፋን ፍቅር ያጣጣምንባት፣ ሲኖረን በቢራ ሳይኖረን በፒን ድብን ብለን ምታቸው ጌታቸው (ይሁዳ) እንደሚለው "እንደ ድራገን እሳት እየተፋን" በሊት ወደ ግቢ የገባንባት የትዝታችን ማሀተብ ናት። መንገዷን ከአርባምንጭ ከወጣሁ ከ10 አመት በኋላ ተመልሼ ሄጄ አላገኘኋትም። አካባቢው ለምቷል። በኔ ልብ ውስጥ ግን እንደነበረች አለች። አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ከደረስኩ ሶስት ቀን በኋላ ሴጣን ሰፈር የሚገኝ ዶርም መመደቤን አወኩ። ከ Alex Log Out እና Sami Agip ጋ ዶርማችንን ለማየት በሄድንበት ነበር Akaakayyuu Tolasaa ወይም ሶልን የተዋወኩት። ከዛች ቀን ጀምሮ እኔና ሶል ጓደኛሞች ሆንን። ሴጣን ሰፈር መጨረሻው ብሎክ ውስጥ ተደራራቢ አልጋችን ላይ እኔ ከላይ ሶል ከታች ነበር የምንተኛው። ሴጣን ሰፈር ከመሬት ተነስተው ስያሜውን እንዳልሰጡት የገባኝ አንድ ጎረምሳ ሴጣን ሶልን ማጨናነቅ የጀመረ ጊዜ ነው።አንድ ቀን እኔና ሶል ስንዘምር አመሸን። ከዘመርናቸው የማስታውሰው፡ገናና የኛ እየሱስ አቻ አይገኝለት እንደሞተ አልቀረም ከቶ አለ በሰማያት ማን ይቃወመናል ዛሬ በደሙ ዋጅቶናል ትንሳኤውን ልናወራ በገና አንስተናል የሚል የ80ዎቹ መዝሙር አንዱ ነበር። ጎረምሳው ሴጣን ለካ በጣም ተቃውሞናል። ሁሉም እስከሚተኛ አድፍጦ ጠበቀ። ሶል አገር ሰላም ብሎ በተኛበት እላዩ ላይ ሰፈረ። ሶል አንዳች ነገር እላዩ ላይ ሲያፍ ተሰማው። ከላዩ አሽቀንጥሮ ለመጣል እና ለመነሳት ጉልበት አጠረው። ሴጣኑን መደብደብ ፈለገ ግን እንዴት? መሳደብ እንኳ ፈልጎ ጉሮሮ አልታዘዝ አለው። ታገለ...ታገለ...በመጨረሻም ሴጣኑ ከላዩ ላይ ወርዶ ፊት ለፊቱ ባለ ቁምሳጥ አልፎ ተሰወረ። "ቀዝቃዛው...ቀዝቃዛው" አለኝ ከእንቅልፌ ለመቀስቀስ እየወዘወዘኝ። ባንኜ ሶልን ሳየው ቆሌው ተገፏል። "ምንድነው?" አልኩት። "ድሙ ምለየው ቀዝቃዛው። ዱካክ እላዬ ላይ ሰፍሮ ሊገለኝ!..አነቀኝ... በቦቅስ ልገባለት ስል እጄን ያዘኝ...የመጨረሻ ድሙ ምለየው" እያለ ካብራራልኝ በኋላ "በዚ በኩል ነው የሄደው ስለዚህ እዚጋ መተህ ተኛ" ብሎኝ አንድ ሜትር አልጋ ላይ እኔ ሴጣኑ ሄዷል ባለበት አቅጣጫ እሱ በጥግ ሆነን ተኛን። በማግስቱ "ውስጤ ንፁህ ስለሆነ ሴጣኑ እኔን አልነካኝም" ስለው ሶል "አይ ቀዝቃዛው ዋናው ሴጣን አንተ አደለህ እንዴ...ትናንሾቹ ይፈሩሀል" አለኝ። ሴጣኑ በዛው አልቀረም ለጓደኛዬ ከለላ በመሆኔ ቂም ይዞ ከርሞ ከቀናት በኋላ ጥቃት ሰነዘረ። ልክ ሶልን እንዳደረገው ያንገላታኝ ያዘ። እኔ ግን ከመታገል ይልቅ ጉዳዩን ለፈጣሪ ትቼ ላሽ ማለትን መረጥኩ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ለሽ ብዬ ተኛሁ። ሴጣኑ ተስፋ ቆርጦ ሄደ ከዛ አልተመለሰም። በኔና ሶል መሀል ያለው ልዩነት ይህ ነው። ሶል ገና በልጅነቱ ሀገር ተደፈረች ሲባል እኩዮቹ በኮባ ጥይት በምንጫወትበት እድሜ አገሩን ሊያድን የዘመተ ወታደር ነው። በኢትዩ ኤርትራ ጦርነት ዘምቶ ለሀገሩ የደማ የቆሰለ ሰው ነው። እናም በወቅቱ ለነገሮች የነበረው ምላሽ ወታደራዊ አቋም የቀላቀለ ነበር። ለሴጣንም ቢሆን ቡጢ ነበር ሚሰነዝረው። እኔ ከእየሱስ ጋ ትኩስ ፍቅር ላይ ነበርኩ። መፅሀፍ ቅዱስ መዝናኛዬም፣ መመሰጫዬም ነበር። በሰአቱ ጦር ሜዳ እንኳን ወስደው ቢያስቀምጡኝ በጥይት ሳይሆን በእምነት የምዋጋ አይነት ነበርኩ። እኔና ሶል በዚህ ጠብደል ልዩነታችን ዙሪያ አውርተን... አውርተን አንድ አይነት ልንሆን እንደማንችል ተረድተን አንዳችን ሌላችንን በመቀበል ነበር ምንኖረው። የሴጣን ሰፈር ኑሮአችን በሶል የጦር ሜዳ ታሪኮች፣ በ Tijan Aliyi Edeo እና በኮንሰፕት(የሰው ስም ነው) ቀልዶች፣ በፉአድ ዘፈኖች፣ በይሁዳ ግጥሞች፣ በ Rabuma Shiferaw እና Fitsum Asfaw ፀሎት ደምቆ አለፈ። ተመራቂ ተማሪዎች ሳለን አዘውትረን እንጠጣ ነበር። አንድ ቀን እኔና ሶል በጠጅ ክልትው ብለን ወደ ግቢ ለመመለስ ታክሲ ተራ ሄደን መጠበቅ ጀመርን። ነገር ግን እስከ ለሊቱ ስድስት ሰአት ወፍ የለችም። "ምን ይሻላል" አልኩት። "ጣጣ ምለየው በግር እንቁሰው" አለኝ። አደገኛ ውሳኔ እንደሆነ ተሰማኝ ነገር ግን አማራጭ አልነበረም። ጉዟችንን እንደጀመርን ሌላ ሁለት የግቢ ልጆች እንደኛ ተስፋ ቆርጠው በእግር ለመሄድ ወስነው አገኘናቸው። ከሲቀላ ግቢ ድረስ የአምስት ኬሎ ሜትር ጉዞ ተጀመረ። ጉዞው ምንግዜም ሁለት ምዕራፍ ነው ሚኖረው፡ ከኩልፎ በፊትና ከኩልፎ በኋላ! ከኩልፎ በፊት ሳቅ ጨዋታ ደራ። እንቀልዳለን፣ እንዘፍናለን፣ እንተቃቀፋለን፣ እንሰዳደባለን...ወዘተረፈ። የኩልፎን ድልድይ ከተሻገርን በኋላ ጨለማው ድቅድቅ አለ። ከኋላችን አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ከፊት ለፊታችን ረጅም እና አስፈሪ መንገድ፣ በግራና ቀኛችን መንገዱን ከሙዝ እና ጥጥ ማሳ የሚለዩት ዛፎች መደዳውን ተደርድረዋል። በኩልፎ እና በግቢ መሀል ልማት የምትባል መንደር አለች። የልማት ማጅራት መቺዎች በዛ ድቅድቅ ጨለማ ቢያገኙን ፓንታችንን ሳይቀር ሙልጭ አርገው ነው ሚዘርፉን። በጩቤ ሊወጉንም ይችላሉ። ብቸኛው አማራጭ ግን ልማትን አቋርጦ ማለፍ ነው! የተቀረውን ደግሞ ለፈጣሪ መተው። እኔ "ፈጣሪ አለ። ይጠብቀናል" ብዬ አሰብኩ። ሶል ግን ተቀየረ። ድንገት ወታደሩ ሶል ራሱን ገለጠ። "አሁን ጠላት ወረዳ ገብተናል። ሁላችሁም መሳሪያችሁን አቀባብላችሁ ያዙ" አለ ድንጋይ ከመሬት እያነሳ ሌሎቻችንንም እየጋበዘ። ሁሉም ድንጋይ ያዙ። ሶል ዞሮ ሲመለከተኝ 'አልታጠኩም'። በጣም ተናደደ። "ቀዝቃዛው ጦር ሜዳ ገብተህ እየሱስ ይዋጋልኛህ ብለህ እንዳጠብቅ። ጠላት አድፍጦ እየጠበቀን ነው! ወደ ደጀን እስከምንደርስ ሁሉም መቶኮስ አለበት" አለኝ። የቀጠለው ንግግር፡ እኔ፡ እኔ ድንጋይ ሳይሆን አምላክ ነው ሚጠብቀኝ ሶል፡ ድንጋይ አይደለም መሳሪያ ነው እኔ፡ ምንም በለው። አምላኬ ከምንም ነገር በላይ ይጠብቀኛል ሶል፡ ለምንድነው የሰራዊቱን ሞራል የምትገለው! ብትታጠቅ ምን ትሆናለህ እኔ፡ የእግዚአብሄርን ቃል ታጥቂያለሁ በቃላት ምልልሳችን መሀል መንገድ ላይ ካገኘናቸው ልጆች መሀል አንዱ በኔ እምነት ተማረከ። በጁ የነበሩትን ድንጋዮች አሽቀንጥሮ ጣለ። ሶል በጣም ተበሳጨ። የተቀረውን አንድ ታጣቂ "ቅኝት አድርግ። እነዚን አማኞች በሰላም ግቢ ማድረስ አለብን" እያለ እየተሳለቀብን የግቢ አጥር ጋር ደረስን። እኛ በተማርንበት ጊዜ የትም ውለህ ወደግቢ የመመለሻ ሰአት ማታ አራት ሰአት ነበር። እኛ ግቢው አጥር ጋ ስንደርስ ከምሽቱ ሰባት ሰአት ሆኗል። ስለዚህ በአጥር ሾልከን መግባት ወይ መታወቂያ ለጥበቃዎች አሲዘን መግባት ነበሩ አማራጮቻችን። ነገር ግን ከመሀከላችን መታወቂያ ያልያዝን ነበርንና በአጥር ለመግባት ወሰንን። ሶል ወታደራዊ አመራር መስጠቱን ቀጠለ። የአጥሩን ሽቦ በእግሩ ወደታች በእጁ ወደላይ ወጥሮ እየሾለክን ስናልፍ "አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት" እያለ ቆጠረን። ከአጥሩ በኋላ በቁጥቋጦ እና እሾክ የተሞላ ስለነበር ቀስ እያልን እንራመዳለን። ልክ የዩኒቨርስቲው ህንፃዎች ብርሀን መታየት ሲጀምር ሶል "አሁን ዋናው የጠላት ቀጠና ውስጥ ነን። ከጠላት እይታ ለመሰወር ያለው አማራጭ አንድ ነው" ብሎ አፈጠጠ። "ምን"? ስለው። "ትል አካሄድ" አለ። ሳቄ ባፍ ባፍንጫዬ ተናነቀኝ። ግን ለምን ሳክ በሚል የሚቀሰቀሰውን ፀብ በመፍራት ዋጥ አደረኩት። ወዲያው ትል አካሄድ እንዴት እንደሆነ በደረቱ እየተሳበ ካሳየን በኋላ እንዲህ ሲል አስጠነቀቀኝ፡ "ቀዝቃዛው ስዞር ቆመህ ባይህ ያበቃልናል። ይሄ ሲሪየስ ሁኔታ ነው" አለ ጓ ብሎ። ለአስር ደቂቃ ያክል በደረት እየተሳብን ስንጓዝ ቆይተን፣ እጃችን በእሾክ ተነድሎ፣ ልብሳችን አፈር ልሶ ቁጥቋጦውን ጨርሰን ልክ ወደመንገድ ስንወጣ የግቢ ጥበቃዎች ያዙን። 🙏🙏🙏 በናንተው ጥያቄ መሰረት "ትል አካሄድ"ን ሳልጨምር ሳልቀንስ ተርኬያለሁ። ከዚ በኋላ መክሊቴ ወደሆነው ስነ ስዕል ተመልሻለሁ። እና ደሞ ሼር አርጉ! ምንድነው? እኔ ለትውልድ የሚተላለፉ ስዕሎችን እየሰራሁ እንዴት ቢያንስ ሌሎች እንዲያዩ እንዲያነቡ መጋበዝ ይከብዳችኋል?